The first full-fledged interest-free bank in Ethiopia

ዘምዘም ባንክ በ2025/26 በጀት ዓመት ከታክስና ከልዩ ልዩ ተቀናሾች በፊት 1.8 ቢሊዮን ብር በላይ አተረፈ፣ ጠቅላላ ሀብቱም ከ30 ቢሊዮን ብር በላይ ደረሰ

በአዲስ አበባ በሚገኘው አድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በተካሄደው የባንኩ 6ኛ መደበኛና 5ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ፤ በርካታ የባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተወካዮች እና የሃይማኖት አባቶች በተገኙበት፣ ባንኩ በተጠናቀቀው 2025/26 በጀት ዓመት ያስመዘገባቸው ዋና ዋና የሥራ አፈጻጸም ውጤቶችና ስኬቶች ለባለድርሻ አካላት ቀርቧል።

​ዘምዘም ባንክ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተለያዩ ስኬቶችን ከማስመዝገቡም በላይ፣ ለቀጣይ ዕድገቱና ስኬታማ አፈጻጸሙ የሚያግዙ ጠንካራ መሠረቶችን የጣለበት ዓመት እንደነበር ከባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ናስር ዲኖ ዝርዝር ማብራሪያ መረዳት ተችሏል። ባንኩ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች በጽናት በማለፍ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የሚያበረታቱ ውጤቶችን ማስመዝገቡም ተገልጿል። የተጠናቀቀው በጀት ዓመት እስካሁን ከነበሩት ጉባዔዎች ሁሉ ባንኩ ወደ ስራ የገባበትን 5ኛ ዓመት ክብረ በዓል እያከበረ በሚገኝበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መሆኑ ለየት ያደርገዋል በማለት ያለፉትን የስራ ዓመታት መለስ ብለው ያስታወሱት ቦርድ ሰብሳቢው፣ ያለፉት 5 ዓመታት በርካታ ውጣ ውረድ እና ተግዳሮቶችን አሸንፎ ከማለፍ እና ስኬቶችን ከማስመዝገብ አኳያ የራሳቸውን አሻራ እንዳሳረፉ አስታውሰዋል፡፡

​የዘምዘም ባንክ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ናስር ዲኖ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ባንኩ በ2025/26 በጀት ዓመት ከታክስ እና ከልዩ ልዩ ተቀናሾች በፊት ከ1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡንና ጠቅላላ ሀብቱም 30 ቢሊዮን ብር መሻገሩን አብራርተው፤ የተገኘው ውጤት ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር የባንኩን የላቀ ደረጃ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣይ የተሻለ የሥራ አፈጻጸምና የትርፍ ዕድገት መሠረት የጣለ መሆኑንም ገልጸዋል።

​በጉባዔው ላይ በባንኩ የረጅም ጊዜ ዕድገት እና የካፒታል አቅም ማጠናከሪያ ላይ ትኩረት ያደረጉ ታሪካዊ ውሳኔዎች በባለአክሲዮኖች በሙሉ ድምፅ ፀድቀዋል፦

​የትርፍ ክፍፍልን በአክሲዮን የማሳደግ አማራጭ፦ ባለአክሲዮኖች የዚህን ዓመት የትርፍ ክፍፍል በጥሬ ገንዘብ ከመውሰድ ይልቅ፣ የራሳቸውን የአክሲዮን ድርሻ በቀጥታ ለማሳደግ እንዲችሉ በሙሉ ድምፅ ተወስኗል። ይህም የባለአክሲዮኖችን ለባንኩ ያላቸውን ከፍተኛ ቁርጠኝነትና የባንኩን ማደግ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

ባንኩ የወደፊት የፋይናንሲንግ አቅሙን እና የገበያ ተወዳዳሪነቱን ይበልጥ ለማጎልበት የባንኩ የተፈቀደ ካፒታል (Authorized Capital) ወደ 15 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ በባለፈው አመት ጠቅላላ ጉባኤ መወሰኑ ይታወቃል። በዚህም መሰረት አሁን ላይ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ብር 5.64 ቢሊዮን ደርሷል።

​በተጨማሪም፣ ባንኩ በ2026/27 በጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት አመርቂ የስራ ክንውን ማስመዝገቡን ጠቅሰው፤ ለቀጣይ ዕድገት የተያዘውን ከፍተኛ የስኬት ተስፋ የሚያመለክት መሆኑን ገልጸው ለዚህ ስኬት የባለአክሲዮኖችና የመላው ሠራተኛ የጋራ ጥረትና ቁርጠኝነት የማይተካ ሚና እንዳለውም አስምረውበታል።

​የዘምዘም ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሊካ በድሪ በበኩላቸው፣ ለተመዘገበው አመርቂ ውጤት የደንበኞችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ፣ የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን፣ የዘመኑን የቴክኖሎጂ እድገት መጠቀምና ለደንበኞች ፍላጎት የሚመጥን ቀላል፣ ቀልጣፋና ተደራሽ አገልግሎት መስጠት ወሳኝ ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል። ባንኩ በተጨማሪም የሥራ ሂደቶችን በማሻሻልና ዘመኑን በዋጁ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመታገዝ በተሻለ የአመራር አቅጣጫ፤ በአነስተኛ ወጪ የተሻሉ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።

​በመጨረሻም፣ በቀረበው ሪፖርትና በተለያዩ የውይይት ርዕሶች ላይ ባለአክሲዮኖች የተለያዩ አስተያየቶችንና ገንቢ ሐሳቦችን አቅርበዋል። ማብራሪያ በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችም ከመድረኩ በቂ ምላሽ ተሰጥቶ ጉባዔው በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል።

ዘምዘም ባንክ
የማይነጥፍ የእድገት ምንጭ!


Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

  • About Us
  • Products & Services
  • Media